ታይፈስ በኣንድ ወይም ከዚያን በላይ ባሉ ሪኬቲሲያል ባክቴሪያ አማከኝነት የሚተላለፍ በሽታ ነዉ። ቁንጫ፣ ቅማል፣ ትኋንና ምስጥ( ማይትስ) ሰዉን በሚነክሱበት ወቅት ህመሙን ያሰተላልፋሉ። እነዚህን ባክቴሪያ የያዙ ተዋሲያን አንድን ሰው ሲነክሱ ታይፈስ የሚያስከትሉ ባክቴሪያዎችን ያስተላልፋሉ። የተነከሱበትን ቦታ ሲያኩ ቆዳዎን የበለጠ ስለሚከፈት ባክቴሪያዎቹ ወደ ደም ስርጭትዎ የበለጠ እንዲደርሱ ያስችላቸዋል። በደም ውስጥ ከገባ በኋላ ባክቴሪያው እንደገና መባዛት እና ማደግ ይቀጥላል።
ሦስት የተለያዩ የታይፈስ ዓይነቶች አሉ፡- እነርሱም
· የወረርሽኝ የሚያስከትለዉ (ቅማል- ወለድ) ታይፈስ
· ሥር የሰደደ ታይፈስ የሚያስከትለዉ (ሙሪን ታይፈስ)ና
· ስክራብ ታይፈስ ናቸዉ።
በየትኛዉ የታይፈስ አይነት እንደተያዙ የሚወሰነዉ በየትኛዉ የባክትሪያ ተሸካሚ ተዋሲያን ( አርትሮፖድስ) እንደተነከሱ ሲታወቅ ነዉ። አርትሮፖድስ በተለምዶ ለዓይነታቸው ልዩ የሆነ የታይፈስ ዝርያ ተሸካሚዎች ናቸው። የታይፈስ ወረርሽኝ በአብዛኛው የሚከሰተው በማደግ ላይ ባሉ አገሮች ወይም በድህነት፣ የንጽህና ጉድለትና ሰዎች ተጨናንቀዉ ወይም ተፋፍገዉ በሚኖሩባቸዉ አካባቢዎችና ስፍራ ነው። በታይፈስ በሽታ ተይዘዉ ካልታከሙ ኢንፊክሽኑ ወደ ከባድ ችግሮች ሊያመራ ይችላል፤ ለሞትም ሊዳርግ ይችላል። ስለሆነም ታይፈስ እንዳለብዎ ከተጠራጠሩ የህክምና ባልሙያዎን ማማከር አስፈላጊ ነው።
የህመም ምልክቶች
የታይፈስ የህመም ምልክቶች መታየት የሚጀምሩት የታይፈስ ባክቴሪያ ወደ ሰውነትዎ ከገባ ከ10 ቀናት እስከ 2 ሳምንታት ዉስጥ ነዉ። የህመም ምልክቶቹም
· ብርድ ብርድ ማለት
· ትኩሳት
· የራስ ምታት
· ጉንፋን ሲይዝዎ እንደሚሰማዎ አይነት የጡንቻ ላይ ህመም
· ሌሎች የህመም ምልክቶች ከታዩ በኃላ ቆይቶ የሚመጣ የሰዉነት ላይ ሽፍታ
· ማቅለሽለሽ የሆድ ህመም
· ማስታወክ
· ሳል
የታይፈስ ምክንያቶች
ነፍሳት እና ሌሎች ጥገኛ ተህዋሲያን እርስዎን ሲነክሱ በሰገራቸዉ ዉስጥ ያለዉን ሙሪን ታይፈስንና ተላላፊ የሆነዉን የታይፈስ አይነት( ኢፒዴሚክ ታይፈስ) የሚያስተላልፉ ባክቴሪያዎች በቆዳዎ ላይ ይተዉታል
· በነፍሳት የተነከሰዉን ቦታ ሲያኩ በባክቴሪያ የተበከለውን ሰገራ በነፍሳት ንክሻ ወይም በሌላ ምክንያት በቆዳዎ ላይ ክፍት በሆኑ ቁስሎች ባክቴሪያዉን ያሰራጩታል። በዚህ ምክንያት የታይፈስ ባክቴሪያን ወደ ደምዎ ውስጥ ያስገባሉ።
· ስክራብ ታይፈስ የሚባልዉ ደግሞ የንክሻውን ቦታ ባያኩትም በባክቴሪያው የተበከለው ምስጥ (mites) በሚነክስዎ ወቅት ሊያዙ ይችላሉ።