ክፍል አንድ
ቲቢ በዋነኝነት ሳንባን የሚያጥቃ ከፍተኛ የጤና ጉዳት ሊያደርስ የሚችል ከባድ ተላላፊ በሽታ ነው። የሳንባ ነቀርሳን የሚያመጣው ባክቴሪያ በሳል እና በማስነጠስ ወደ አየር በሚለቀቁ ትንንሽ ጠብታዎች ከሰው ወደ ሰው ይተላለፋል።
ቲቢ ማይኮባክቴሪየም ቲዩበርክሎሲስ በሚባል ባክቴሪያ የሚከሰት ሲሆን ብዙውን ጊዜ በሳንባዎ ላይ ተጽዕኖ ያሳድራል። ቲቢ ከሰው ወደ ሰው በትንፋሽ አማካይነት ይተላለፋል። የሳንባ ቲቢ ያለባቸው ሰዎች ሲያስሉ፣ ሲያስነጠሱ ወይም አክታቸዉን ሲተፉ የቲቢ ጀርሞቹን ወደ ሚተነፍሱት አየር ያስገባሉ ወይም ይረጫሉ። አንድ ሰው ይህን በባክቴሪያ የተበከለ አየር በሚተነፍስበት ወቅት በቲቢ ሊያዝ ይችላል።
ከዓለም ህዝብ አንድ አራተኛ የሚሆነው የቲቢ ኢንፌክሽን አለበት፤ ይህም ማለት ሰዎች በቲቢ ባክቴሪያ ተይዘዋል ነገር ግን እስካሁን በቲቢ በሽታው አልታመሙም እናም በሽታዉን ወደ ሌላ ሰዉ ሊያስተላልፉ አይችሉም ማለት ነዉ።
በቲቢ ባክቴሪያ የተያዙ ሰዎች ከ5-10% በህይወት ዕድላቸው በቲቢ የመታመም እድል አላቸው። ኤች አይ ቪ በደማቸው ውስጥ ያለ፣ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት ወይም የስኳር በሽታ ያላቸዉ ወይም ትንባሆ የሚያጨሱ ሰዎችና የበሽታ መከላከል አቅማቸው የተዳከመ ሰዎች በቲቢ የመታመም እድላቸው ከፍ ያለ ነው።
እንደ የአለም ጤና ድርጅት መረጃ በፈረንጆቹ 2020 1.5 ሚሊዮን ሰዎች በቲቢ ምክንያት ለህልፈተ ህይወት ተዳርገዋል። ቲቢ 13ኛው የሞት መንስኤ እና ከኮቪድ-19 ቀጥሎ ሁለተኛው ተላላፊ ገዳይ በሽታ ነው (ከኤችአይቪ/ኤድስ በላይ ማለት ነዉ)። በዚሁ ዓመት 10 ሚሊዮን ሰዎች በቲቢ በሽታ ተይዘዋል።
ቲቢ ሊታከምና ልንከላከለዉ የሚንችለዉ ህመም ነዉ ።
የህመም ምልክቶች
ምንም እንኳን ሰውነትዎ የቲቢ በሽታ አምጪ ተህዋስያንን ሊይዝ ወይም ሊደብቅ ቢችልም የበሽታ መከላከል ስርዓትዎ ብዙውን ጊዜ በቲቢ ከመታመም ይከላከልልዎታል። ቲቢ ላተንት ቲቢና አክቲቭ ቲቢ ተብሎ የከፈላል።
· ተደብቆ የሚቆይ ወይም ላተንት ቲቢ፡- የቲቢ ኢንፌክሽን አለዎት፣ ነገር ግን በሰውነትህ ውስጥ ያሉት ባክቴሪያዎች እየተራቡ ስለይደሉ ምንም አይነት የህመም ምልክት አያሳዩም። ይህ የቲቢ አይነት ተላላፊ አይደለም፤ ነገር ግን ወደ አክቲቭ ቲቢ ሊለወጥ ይችላል።
· አክቲቭ ቲቢ፡- ወይም የቲቢ ህመምም ተብሎ ሊጠራ ይችላል። ይህም ሰዎች የቲቢ ህመም ምልክቶች ይኖሩዋቸዋል ፤ አብዛኛዉ ጊዜም ከህመምተኛዉ ወደ ሌሎች ሊዛመት ይችላል። ይህ በቲቢ ባክቴሪያ ከተያዙ ከሳምንታት ወይም ከዓመታት በኋላ በሽታዉ ሊከሰት ይችላል።
የአክቲቭ ቲቢ የህመም ምልክቶች
· ከሁለት ሳምንትና ከዚያን በላይ ሳል
· አክታ ያለዉ ወይም ደም የቀላቀለ ሳል
· የደረት ህመም ወይም ሲተነፍሱና ሲያስሉ የደረት ላይ ህመም
· ያልታቀደ የሰዉነት ክብደት መቀነስ
· ድካም
· ትኩሳት
· ማታ ማታ ማላብ
· ብርድ ብርድ ማለት
· የምግብ ፍላጎት መቀነስ ናቸዉ
ቲቢ ኪላሊትን፣ የጀርባ አጥንትንና አንጎልን ጨምሮ ከሳንባ ዉጪ ሌሎች የሰዉነት ክፍሎችንም ሊያጠቃ ይችላል። ከሳንባ ዉጪ ቲቢ ሲከሰት የህመም ምልክቶቹ እንደተጠቁት የሰዉነት አካል ይለያያል።