ክፍል ሁለት
ሁሉም ወይም ማንኛዉም ሰዉ ለቲቢ ተጋላጭ ቢሆንም የተወሰኑ ነገሮች ወይም ምክንያቶች ቲቢ የመያዝን ዕድልን ይበልጥ ይጨምራሉ። እነርሱም
1. የበሽታ መከላከል አቅም መዳከም
ጤናማ የበሽታ መከላከያ ስርዓት ብዙውን ጊዜ የቲቢ ባክቴሪያዎችን በተሳካ ሁኔታ ይዋጋል ፤ ነገር ግን፣ በርካታ ሁኔታዎችና መድሃኒቶች የእርስዎን በሽታ የመከላከል ስርዓት ሊያዳክሙ ይችላሉ፣ ከእነዚህም መካከል፡-
· ኤች አይቪ ኤድስ
· ስኳር ህመም
· ከፍተኛ ደረጃ የደረሰ የኩላሊት ህመም
· ኬሞቴራፒ የመሰሉ የካንሰር ህክምናዎች
· የአካል ንቅለተከላ ሲደረግ የሚሰጡ መድሃኒቶች
· ስር የሰደዱ ህመሞችን ለማከም የሚሰጡ መድሃኒቶች
· የምግብ ዕጥረት ወይም ከመጠን በታች የሆነ የሰዉነት ክብደት መኖር
· በእድሜ መግፋት አሊያም በለጋነት ዕድሜ የመሳሰሉት ናቸዉ።
2. ሌሎች ምክንያቶች
· አደንዛዥ ዕፅ መጠቀም፦ በደም ስር የሚወሰዱ አደንዛዥ መድኃኒቶች ወይም ከመጠን በላይ አልኮሆል መጠጣት የሰውነትን በሽታ የመከላከል ስርዓትን በማዳከም ለሳንባ ነቀርሳ የበለጠ ተጋላጭ ያደርግዎታል
· ሲጋራ ማጨስ፦ ሲጋራ ማጨስ በቲቢ የመያዝንንና በህመሙ ለህልፈተ ህይወት መዳረግ እድልን በእጅጉ ይጨምራል።
· በጤና ተቋም ዉስጥ የሚሰሩ ከሆነ፦ ከታመሙ ሰዎች ጋር አዘውትሮ መገናኘት ለቲቢ ባክቴሪያ የመጋለጥ እድልን ይጨምራል። በተቃራኒው ማስክ ማድረግና አዘውትሮ እጅን መታጠብ አደጋዎን በእጅጉ ይቀንሳል።
· በቲቢ ከተያዘ ሰዉ ጋር በአንድ ላይ መኖር፦ ቲቢ ካለበት ሰው ጋር የቅርብ ግንኙነት ማድረግ በቲቢ የመያዝ አደጋዎን ይጨምራል።
ቲቢ ሊያመጣዉ የሚችለዉ የጎንዮሽ ጉዳት
ቲቢ ካልታከመ ለህልፈተ-ህይወት ሊዳርግ ይችላል። ሊያመጣቸዉ ከሚችላቸዉ የጎንዮሽ ጉዳቶች ዉስጥ
· የአከርካሪ ህመም፦ የጀርባ ህመምና ግትር ማለት/መጠንከር የቲቢ የተለመዱ ችግሮች ናቸው
· የመገጣጠሚያ ላይ ጉዳት፦ በቲቢ ምክንያት የሚከሰት የመገጣጠሚያ መጎዳት( አርትራይትስ) በጀርባና በጉልበት መገጣጠሚያዎች ላይ በብዛት ይከሰታል
· የአንጎል የሚሸፍናዉ ሽፋን ማበጥ ( የማጅራት ገትር)፦ ይህ ለተወሰነ ጊዜ አሊያም የማያቋርጥ የራስ ምታት ይኖረዋል፡።
· የጉበትና ኩላሊት ጉዳት፦
· የልብ ችግር፦ አልፎ አልፎ ቲቢ የልብ ሽፋንን ስለሚያጠቃ የልብ ሽፋን መቆጣትና ፈሳሽ እንዲጠራቀም ስለሚያደርግ የልብ ደም መርጨት ላይ ጫና ያሳድራል።
ቲቢን መከላከል
ተደብቆ የሚቆይ ወይም ላተንት ቲቢ ካለዎ ወደ ቲቢ በሽታ (አክቲቭ ቲቢ) እንዳይለወጥቦት ህኪምዎ መድሃኒት እንዲወስዱ ሊያደርግዎ ይችላል። እንደሚያዉቁት አክቲቭ ቲቢ ብቻ ነዉ ከሰዉ ወደ ሰዉ የሚታላለፈዉ።
ቤተሰብንና ጓደኞችዎን ለመከላከል
አሁን የቲቢ ህመም ታማሚ ከሆኑ በሽታዉን ወደ ሌላ ሰዉ እንዳይተላለፍ ለማደርግ የቲቢ መድሃኒትዎን ለተውሰኑ ሳምንታት መዉሰድ አለብዎ። ቤተሰብዎንና ጓደኖችዎን ከቲቢ ለመከላከል
· በቤት መቆየት፦ በመጀመሪያዎቹ የሕክምና ሳምንታት ወደ ሥራ ወይም ትምህርት ቤት አይሂዱ ወይም ከሌሎች ሰዎች ጋር በአንድ ክፍል ውስጥ አይተኙ
· ክፍልዎን ማናፈስ፦ ቲቢን የሚያመጡ ጀርሞች አየር በደንብ በማይዘዋወር ወይም በማይንቀሳቀስባቸው ትናንሽ የተዘጉ ቦታዎች ላይ በቀላሉ ይሰራጫሉ።የዉጪዉ አየር በጣም ቀዝቃዛ ካልሆነ በስተቀር መስኮቶችን ክፍት ያድርጉ። ከተቻለም ቬንትሌተር በመጠቀም ቤት ዉስጥ ያለዉን አየር ወደዉጪ እንዲወጣ ማድረግ ይችላሉ።
· አፍና አፍንጫዎን መሸፈን፦ በሚስቁበት፣ በሚያስሉበት ወይም በሚያስነጥሱበት ጊዜ አፍዎንና አፍንጫዎን በሶፍት፣ መሃረብ ወይም ማስክ መሸፈን ።አፍዎን ለመሸፈን የተጠቀሙበትን ቆሸሸውን ሶፍትም ይሁን ሌላ ነገር በአግባቡ ያስወግዱ፤ በየቦታዉ አይጣሉ።
· ማስክ ያድርጉ- በመጀመሪያዎቹ ሶስት ሳምንታት የህክምና ወቅት ከሌሎች ሰዎች ጋር በሚሆኑበት ጊዜ ማስክ ማድረግ የበሽታውን ተጋላጭነትና ስርጭት ለመቀነስ ይረዳል።