የደም ቅዳዎች ኦክሲጅንና የላሙ የምግብ ንጥረነገሮችን የያዘን ደም ከልብ ወደ ሁሉም የሰዉነታችን ክፍሎች የሚያደርሱ የደም ስሮች ወይም ቧንቧዎች ናቸዉ። የዉጨኛዉ የደም ቅዳ የደም ቧንቧዎች ችግር የሚከሰተዉ በእጅና እግር የደም ቅዳ የደም ቧንቧዎች ላይ ነዉ።
ጤናማ የደም ቅዳ የደም ቧንቧዎች ዉስጣቸዉ ለስላሳ ሲሆን ደም እንዳይረጋና የደም ዝዉዉሩ ሳይታወክ በትክክሉ አንዲጓጓዝ የሚያደርግ ነዉ። የደም ቅዳ የደም ቧንቧዎች ችግር ሲከሰት የደም ቧንቧዎቹ ዉስጥ ቀስ በቀስ የሚጋገረዉ ነገር( ፕሌክ) የደም ቧንቧዎቹ በሂደት እየጠበቡ ወይም አንዲዘጉ ያደርጋል። የደም ቧንቧዎች ዉስጥ የሚጋገረዉ ነገር(ፕሌክ) የተሰራዉ ወይም የያዘዉ ስብ፣ ኮሌስትሮልና በደም ቧንቧዎች ዉስጥ የሚዘዋወሩ የደም ሴሎች፣ፕሮቲንና ካልሲየም ነዉ። የደም ቧንቧዎቹ ከጠበቡ ወይም ከተዘጉ ወደ ሰዉነት አካላት የሚሄደዉ የደም ዝዉዉር ስለሚቀንስ ወይም ስለሚቋረጥ የደም ዝዉዉር የተቋረጠበት የሰዉነት ክፍል ለጉዳት ይዳረጋል።
ከዉጨኛዉ ደም ቅዳ የደም ቧንቧዎች ችግር ወይም ህመም ጋር የሚገናኙ ሁኔታዎች
የዉጨኛዉ ደም ቅዳ የደም ቧንቧዎች ችግር ወይም ህመም ሳይታከም ከቆየ በጣም ከባድ የጤና ችግሮችን ሊያመጣ ይችላል። ከነዚህም ዉስጥ
· ድንገተኛ የልብ ጥቃት፦ ወደ ልብ ጡንቻዎች የሚሄደዉ የደም ዝዉዉር ቢቋረጥ የማይሽር የልብ ጡንቻ መጎዳት ችግር ሊከሰት ይችላል
· ስትሮክ፦ ወደ አንጎል የሚሄደዉ የደም ዝዉዉር ሲቋረጥ
· ጊዜያዊ በሆነ የደም ዝዉዉር ማነስ ምክንያት የሚመጣ አደጋ( ትራንዚየንት ኢስኬሚክ አታክ)፦ ወደ አንጎል የሚሄደዉ የደም ዝዉዉር በጊዜያዊነት ሲቋረጥ የሚከሰት ችግር
· ወደ ኩላሊት የሚሄደዉ የደም ቅዳ የደም ቧንቧ ጥበት ወይም ህመም፦ ኩላሊታችንን የሚመግበዉ የደም ቅዳ የደም ቧንቧ ሲጠብ ወይም ሲዘጋ የሚከሰት
· የእግር/እጅ መቆረጥ፦ በከፊልም ይሁን በሙሉ የእግር አልፎ አልፎ ደግም የእጅ መቆረጥ፤ በተለይ የስኳር ህመም ባላቸዉ ሰዎች ላይ
ለዉጨኛዉ ደም ቅዳ የደም ቧንቧዎች ችግር ወይም ህመም አጋላጭ ነገሮች
· ዕድሜ ከ50 አመትና በላይ
· ሲጋራ ማጨስ
· ስኳር ህመም
· የደም ግፊት መኖር
· ከፍ ያለ የኮሊስትሮል መጠን
· የሰዉነት ዉፍረት( በተለይ የሆድ)
· የኩላሊት ህመም
· ዘር፦ አፍሪካ አሜሪካኖች ከሊሎች ዘሮች ይልቅ ሁለት እጥፍ ተጋላጭ ናቸዉ
· በቤይተሰብ ዉስጥ የልብና የደም ቧንቧ ችግር መኖር