የስኳር በሽታ በደምዎ ውስጥ ያለው የግሉኮስ ወይም የደም ስኳር መጠን በጣም ከፍተኛ በሚሆነበት ወቅት የሚከሰት በሽታ ነው። የሰዉነታችን ሴሎች ሀይልና ጉልበት የሚያገኙት ከግሉኮስ ነዉ። ግሉኮስን ደግሞ የምናገኘዉ ከምንመገበዉ ምግብ ነዉ። ግሉኮስን ወደ ሴሎቻችን እንዲገባ የሚያደርገዉ ኢንሱሊን የሚባልዉ ሆርሞን ነዉ። አይነት አንድ የስኳር አይነት ሲኖርዎ ሰዉነትዎ ኢንሱሊን የማምረት አቅሙ ይቀንሳል። አይነት ሁለት የስኳር አይነት ሲኖር ደግም ሰዉነትዎ ኢንሱሊን እያለ መጠቀም አይችልም፤ አንዳንዴ ደግሞ እንደ አይነት አንድ የስኳር አይነት አይነት ሁለትም አንሱሊን ማምረት አይችልም። ይህ የኢንሱሊን እጥረት መኖር አሊያም መጠቀም አለመቻል በደምዎ ዉስጥ ጉሉኮስ( ስኳር) እንዲጠራቀምና መጠኑ እንዲጨምር ያደርጋል።
የስኳር ህመም ሊያመጣዉ የሚችለዉ የአይን ችግር
በደምዎ ዉስጥ የስኳር መጠን ከፍተኛ ሆኖ ከዘለቀ በጊዜ ሂደት በአይንዎ የደም ቧንቧዎችና ሌንስ ላይ ጉዳት ያደርሳል። ይህ በስኳር ህመም ምክንያት የሚከሰት ወደ ከባድ የአይን ችግር ሊያመራ ይችላል፤ ይህም እይታዎን ሊጎዳና አንዳንዴም ዓይነ ስውርነትን ሊያስከትል ይችላል።
አንዳንድ የተለመዱ የስኳር በሽታ የዓይን ችግሮች የሚከተሉት ናቸዉ።
· ዳያቤቲክ ሬቲኖፓትይ፦ ይህ በስኳር ህመም ምክንያት በዋነኛነት አይነስዉርነትን ሊያመጣ የሚችል ችግር ነዉ። ይህ ችግር በአይንዎ ሌንስ ጀርባ ባሉት በሬቲና የደም ቧንቧዎች ላይ ጉዳት ያደርሳል። የደም ሥሮች ሊያብጡ ወይም ደም አይንዎ ሬቲና ላይ እንዲፈስ ያደርጋሉ። ይህ በወቅቱ ካልታከመ የሬቲና መላቀቅ( retinal detachment) አንዲከሰት ያደርጋል።
· ግላኮማ፦ ግላኮማ አይንዎን ከአንጎልዎ ጋር የሚያገናኙ ነርቮች( ኦፕቲክ ነርቮችን) እንዲጎዱ የሚያደርግ ችግር ነዉ። የስኳር በሽታ ግላኮማ እንዲከሰት የሚያደርገዉ በዓይንዎ በፊተኛዉ ክፍል ያሉት የደም ስሮች ሲጎዱና የዓይንዎ ቀለም ክፍል ወይም አይሪስ አጠገብ አዳዲስ የደም ሥሮች ሲያድጉ ነዉ። ይህ የደም ቧንቧዎቹ እንዲዘጉ በማድረግ ፈሳሽ አይንዎ ዉስጥ እንዲጠራቀም በማድራግ የአይንዎ ግፊት እንዲጨምር ያደርጋል።
· የአይን ሌንስ በሞራ መሸፈን( ካታራክት)--ይህ የአይንዎ ሌንስ በሞራ ሲሸፈን ሌንሱ ጉም መስሎ ይታያል። የአይን ሌንስ በሞራ መሸፈን መከሰት እድሜዎ እየጨመረ ሲመጣ መታየት የተለመደ ነዉ። ነገር ግን የስኳር በሽታ ያለባቸው ሰዎች የስኳር በሽታ ከሌለባቸው ሰዎች በበለጠ ሳያረጁ ቀደም ብሎና በፍጥነት በዓይን የሞራ ግርዶሽ የመጋለጥ እድላቸው ሰፊ ነው።
· በስኳር በሽታ ምክንያት የሚከሰት የማኩላር እብጠት( Diabetic macular edema (DME))፦ በሬቲና ውስጥ ያሉ የደም ሥሮች ወደ ማኩላ ውስጥ ደም(ፈሳሽ) ሲያፈሱ የሚከሰት ችግር ነዉ ። ማኩላ የሬቲና ክፍል ሲሆን የጠራ እይታ አንዲኖረን የሚያደርገዉ ክፍል ነዉ
ለስኳር በሽታ የአይን ችግር የመጋለጥ ዕድሉ የሚጨምረዉ ማን ላይ ነው?
የስኳር በሽታ ያለበት ማንኛውም ሰው በስኳር ምክንያት የሚከሰት የዓይን ሕመም ሊይዘዉ ይችላል። ነገር ግን የሚከተሉት ካሉ የችግሩ መከሰት እድል ከፍ ያለ ነው።
· የስኳር ህመም ለረጅም ጊዜ መኖር
· በደምዎ ውስጥ ያለው የስኳር መጠን ወይም የደም ግፊትዎ ላይ ጥሩ ቁጥጥር ሳይኖርዎት ሲቀር
· ነፍሰጦሮች
· የደም ኮሌስትሮል መተን ከፍተኛ መሆን
· ሲጋራ የሚያጨሱ ከሆነ
የህመም ምልክቶች
የስኳር በሽታ ያለባቸው ሰዎች በመጀመሪያዎቹ የህመም ጊዜያት የዓይን ችግሮቹ ብዙውን ጊዜ ምንም አይነት የህምመ ምልክት ላይታይባቸዉ ይችላል። ለዛም ነው ዓይኖችዎ ጤናማ ናቸው ብለው ቢያስቡም መደበኛ የዓይን ምርመራዎች ማድረግ በጣም አስፈላጊ የሚሆነዉ። በተጨማሪም እይታዎ ላይ ክትትል በማድረግ ለዉጥ ሲያዩ ወዲያዉ ህክምና ማድረግ ይገባል።
የሚከተሉት ምልክቶች ካለዎ የህክምና ባልሙያ ማምከር ያስፈልጋል
· በእይታዎ ውስጥ የሚንሳፈፉ ብዙ አዲስ ነጠብጣቦች ወይም ጠቆር ያሉ የሚንሳፈፉ ነገሮች ካዩ
· የብርሃን ብልጭታዎች መታየት
· እንደ መጋረጃ ከፊል እይታዎ ላይ ጥቁር ጥላ መኖር
· የእይታ መቀነስ ወይም መጥፋት
· የአይን ህመም ወይም መቅላት
· የእይታ መደብዘዝ
· ቀለሞችን ለማየት ወይም መለየት መቸገር ናቸዉ።