አይነት 2 ስኳርና ቀደም ብለዉ ሊታዩ የሚችሉ ምልክቶች
ዓይነት 2 የስኳር በሽታ ቀስ በቀስ የሚከሰት ሲሆን በመጀመሪያዎቹ የህመሙ ደረጃዎች ላይ የህመም ምልክቶች ቀላል ያሉ ሊሆኑ ይችላሉ። በዚህ የተነሳ ብዙ ሰዎች የህመም ምልክቶቹን ችላ ሊሉዋቸዉ ይችላሉ።
ቀደም ብለዉ ሊታዩ የሚችሉ የህመም ምልክቶች
1. በተደጋጋሚ የሽንት መሽናት፦ በደም ውስጥ ያለው የስኳር መጠን ከፍ በሚልበት ጊዜ ኩላሊቶቹ ከመጠን በላይ ስኳርን ከደም ውስጥ በማጣራት ለማስወገድ ይሞክራሉ። ይህ በተለይ ምሽት ላይ ባልተለመደ ሁኔታ ሽንት ቶሎ ቶሎ መሽናት ሊያመጣ ይችላል።
2. የዉሃ ጥም መጨመር፦ ከመጠን በላይ ስኳርን ከደም ውስጥ ለማስወገድ በተደጋጋሚ ሽንት መሽናት ይኖራል።ይህም ሰውነት ተጨማሪ ውሃ እንዲያጣ ሊያደርግ ይችላል። ይህ በሂደት የሰዉነት ፈሳሸ ምጣኔን በመቀነስ ለፈሳሽ እጥረት ይዳርጋል። የዉሃ መጥማትንም ይበልጥ ያባብሳል።
3. የረሃብ ( የመራብ) ስሜት ሞኖር፦ የስኳር በሽታ ያለባቸው ሰዎች ብዙውን ጊዜ ከሚመገቡት ምግቦች በቂ ጉልበት አያገኙም። በዚህ ምክንያት ዓይነት 2 የስኳር በሽታ ያለባቸው ሰዎች ምንም ያህል በቅርቡ ቢበሉም ብዙውን ጊዜ የማያቋርጥ ረሃብ ይሰማቸዋል።
4. ድካም፦ ስኳር የሰዉነት መድካምና ማዛል ስሜት ሊያመጣ ይችላል። የስኳር በሽታ ድካም የሚከሰተው ስኳር ከደም ውስጥ ወደ ሰውነት ሴሎች ውስጥ በበቂ መጠን ስለማይዘዋወር ነዉ።
5. የእይታ ላይ ብዥታ፦ በደም ውስጥ ያለው የስኳር መጠን መጨመር በአይን ውስጥ የሚገኙትን ጥቃቅን የደም ስሮች ይጎዳል፤ ይህም የዓይን ብዥታ ያስከትላል። በደም ውስጥ ያለው የስኳር መጠን መጨመር የዓይንዎ ሌንስ እንዲያብጥ ያደርጋል። ይህ የዓይን ብዥታን ሊያስከትል ይችላል። ነገር ግን የደም ስኳር መጠን ሲቀንስ ይሻሻላል።
6. የቁስል ቶሎ ያለመዳን፦ በደም ውስጥ ያለው ከፍተኛ የስኳር መጠን የሰውነትን ነርቮችና የደም ቧንቧዎችን ይጎዳል። ይህም የደም ዝውውርን ይጎዳል። በዚህም የተነሳ ትናንሽ ቁስሎችና የቆዳ መቆረጥ እንኳ ለመዳን ሳምንታት ወይም ወራት ሊፈጅ ይችላል። የቁስል ቶሎ ያለመዳን ደግሞ ይኢንፌክሽን መከሰት አደጋን ይጨምራል።
7. በእጆች ወይም በእግሮች ላይ መጠቅጠቅ፣ መደንዘዝ ወይም ህመም መኖር፦ ከፍተኛ የደም ስኳር መጠን የደም ዝውውርንና ነርቮችን ሊጎዳ ይችላል። ይህ በእጆችና በእግሮች ላይ ህመም ወይም የመደንዘዝ ወይም የመጠቅጠቅ ስሜት ያስከትላል።
8. ቆዳዎ ላይ ጥቁር ነጠብጣቦች ሞኖር፦ በአንገት፣ በብብት ወይም ብሽሽት ላይ የሚፈጠሩ ጠቆር ያለ ቆዳዎች የስኳር ህመም ምልክት ሊሆን ይችላል።
9. የፈንገስ ኢንፌክሽን፦ በደም እና በሽንት ውስጥ ያለው ከመጠን በላይ ስኳር ለፈንጋሶች እንደምግብ ያገለግላል። ይህም የፈንገስ መብዛት ወደ ኢንፌክሽን ሊያመራ ይችላል። የፈንገስ ኢንፌክሽን እንደ አፍ፣ ብልት አካባቢና ብብት ባሉ ሞቃታማና እርጥብ የቆዳ ቦታዎች ላይ የመከሰት አዝማሚያ ይታያል።